ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ በጉመርና በኮሳ የቡና እርሻ ማሳዎች ነው ለሰራተኞቹ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ሰርቶ ያስረከበው።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሳኒ ረዲ ግሩፑ ለሰራተኞች ሁለተናዊ እድገት ያለውን ቁርጠኝነት ጠቅሰው ለሰራተኞች የተገነቡት ቤቶች አዲስ ቴክኖሎጂን የተጠቀሙና ምቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር ሳኒ የድርጅቱ አላማ የሰራተኞችን ደሞዝ ማሻሻል፣ማበረታቻ ሽልማት መስጠትና የስራ ሁኔታን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን የሚወለዱ ህጻናት የነገ የግብርናው ዘርፍ ተመራማሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል።
የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ነጻነት ጋሻዬ በበኩላቸው በሶስት ወራት ጥራት ባላቸው የግንባታ እቃዎች ተገንብተው የተጠናቀቁት ቤቶች ለቀጣይ ስራዎች መነሻ እንደሆኑ ጠቅሰው በቀጣይም ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ተጨማሪ ቤቶችን ለመገንባት 2 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡን ገልጸዋል።
ደ/ር ነጻነት ሆራይዘን ፕላንንቴሽንስ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና እሴት የሆኑትን ተጠያቂነት፣ሃላፊነት፣ግልጸኝነትና ባለቤትነትን መገለጫ አድርጎ እየሰራ አመርቂ ውጤት በማምጣት ላይ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው ሰራተኞችም ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።
የጉመር እርሻ ስራ አስኪያጅ አቶ ዋሲሁን አያሌው የሰራተኛ መኖሪያ ቤት ለዘመናት የቆየ ጥያቄ ነበር። በመሆኑም በራሳችን አቅም ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም 9 አይነት ትይፖሎጅ ያላቸው መኖሪያ ቤቶን በ3 ወር ገንብተን አስረክበናል ብለዋል።
የኮሳ እርሻ ስራ አስኪያጅ አቶ ቡልቱማ ሞርካ በበኩላቸው በኮሳ የተገነቡት ቤቶች የሰራተኞች የቤት ጥያቄን የሚመልሱና ለቀጣይ ስራ የሚያነሳሱ ናቸው ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ በቤት ግንባታው ወቅት ልዩ ትጋት ላሳዩና አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ትልቅ ትልዕኮ አካል የሆነውን የድሬ ቶጎ ደንቢ ወንዝ መሸጋገሪያ ድልድይ በ9.7 ሚሊየን ብር ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
ድልድዩ ለረጅም ጊዜ የማህበረሰብ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የመሰረተ ልማት ጥያቄ የፈታ ሲሆን የልማት እንቅስቃሴዎችንም ያፋጥናል ተብሎ ይጠበቃል።
የጅማ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱ አህመድ የግንባታውን መጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት መሆን በቦታው ተገኝተው ለማህበረሰቡ አብስረዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ መስኮች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ያደነቁት ሃላፊው ሚድሮክ የሀገር ሀብት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀው ይገባል ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በግብርና፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት፣ በሆስፒታሊቲና በንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ ከ80 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረና ከአመታዊ ትርፉ 10 በመቶውን ለማህበራዊ ሃላፊነት የመደበ ተቋም ነው፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ-የሀገር ሀብት




